Numbers 4

ቀዓታውያን

1 እግዚአብሔር (ያህዌ) ሙሴንና አሮንን እንዲህ አላቸው፤ 2“ከሌዋውያን ወገን የቀዓት ዘር የሆኑትን በየጐሣቸውና በየቤተ ሰባቸው ቍጠሩ። 3እንዲሁም በመገናኛው ድንኳን ውስጥ ይሠሩ ዘንድ ለማገልገል የሚመጡትን ከሠላሳ እስከ አምሳ ዓመት የሆናቸውን ወንዶች ሁሉ ቍጠሩ።

4“በመገናኛው ድንኳን ውስጥ የቀዓታውያን ሥራ ንዋየ ቅድሳቱን መጠበቅ ነው። 5ሰፈሩ ሲነሳ አሮንና ልጆቹ ገብተው የሚከልለውን መጋረጃ ያውርዱ፤ የምስክሩንም ታቦት ይጠቅልሉበት፤ 6ከዚያም በአቆስጣው ቍርበት ይሸፍኑት፤ ሙሉ በሙሉ ሰማያዊ የሆነ መጐናጸፊያ በላዩ ላይ ይዘርጉበት፤ መሎጊያዎቹንም በየቦታው ያስገቡ።

7“በገጸ ኅብስቱ ገበታ ላይ ሰማያዊ ጨርቅ ይዘርጉበት፤ በላዩም ላይ ወጭቶች፣ ጭልፋዎች፣ ጽዋዎች፣ ለመጠጥ ቍርባን የሚሆኑትን ማንቈርቈሪያዎች እንዲሁም ሁልጊዜ ከዚያ የማይታጣውን ኅብስት ያስቀምጡ። 8በእነዚህም ላይ ቀይ ጨርቅ ይዘርጉ፤ የአቆስጣውን ቍርበት ደርበውም መሎጊያዎቹን በየቦታቸው ያስገቡ።

9“ደግሞም ሰማያዊ ጨርቅ ወስደው ማብሪያ መቅረዙንና መብራቶቹን፣ መኮስተሪያዎቹንና የኵስታሪ መቀበያዎቹን፣ እንዲሁም ለዚሁ አገልግሎት የሚውሉትን የዘይት ዕቃዎች ይሸፍኑበት። 10ከዚያም ይህንና ከዚሁ ጋር የተያያዙትን ዕቃዎች ሁሉ በአቆስጣ ቍርበት መሸፈኛ ጠቅልለው በመሸከሚያ ሳንቃ ላይ ያስቀምጡት።

11“በወርቅ መሠዊያ ላይ ሰማያዊ ጨርቅ ዘርግተው በአቆስጣ ቍርበት በመሸፈን መሎጊያዎቹን በየቦታቸው ያስገቡ።

12“እንዲሁም በመቅደሱ ውስጥ ለአገልግሎት የሚሆኑትን ዕቃዎች በሙሉ ወስደው በሰማያዊ ጨርቅ በአቆስጣ ቍርበት በመሸፈን በመሸከሚያው ሳንቃ ላይ ያስቀምጡት።

13“ከናሱ መሠዊያ ላይ ዐመዱን ጠርገው ሐምራዊ ጨርቅ ያልብሱት፤ 14ከዚያም ለመሠዊያው አገልግሎት የሚውሉትን ዕቃዎች በሙሉ፣ የእሳት ማንደጃዎቹን፣ ሜንጦዎቹን፣ የእሳት መጫሪያዎቹንና ጐድጓዳ ሳሕኖችን በላዩ ላይ ያድርጉ፤ በእነዚህም ላይ የአቆስጣ ቍርበት መሸፈኛ አልብሰው መሎጊያዎቹን በየቦታቸው ያስገቡ።

15“አሮንና ልጆቹ መቅደሱንና ዕቃዎቹን፣ ንዋየ ቅድሳቱንም በሙሉ ሸፍነው ከጨረሱ በኋላ ሰፈሩ ለመንቀሳቀስ ዝግጁ ሲሆን፣ ቀዓታውያን ለመሸከም ይምጡ፤ እንዳይሞቱ ግን ንዋየ ቅድሳቱን መንካት የለባቸውም፤ ስለዚህ በመገናኛው ድንኳን ውስጥ ያሉትን እነዚህን ዕቃዎች የሚሸከሙ ቀዓታውያን ናቸው።

16“የካህኑ የአሮን ልጅ አልዓዛር በመብራቱ ዘይት፣ ደስ የሚያሰኝ ሽታ ባለው ዕጣን፣ ዘወትር በሚቀርበው በእህል ቍርባንና በቅብዐ ዘይቱ ላይ ኀላፊነት ይኖረዋል፤ እንደዚሁም ማደሪያውንና በውስጡ ያለውን ሁሉ መቅደሱንና ዕቃዎቹን ጭምር ይጠብቃል።”

17 እግዚአብሔር (ያህዌ) ሙሴንና አሮንን እንዲህ አላቸው፤ 18“የቀዓት ጐሣዎች ከሌዋውያን ተለይተው እንዳይጠፉ፤ 19ወደ ንዋየ ቅድሳቱ በሚቀርቡበትም ጊዜ በሕይወት እንዲኖሩ እንጂ እንዳይሞቱ አንተ ይህን አድርግላቸው፤ አሮንና ልጆቹ ወደ መቅደሱ ይግቡ፤ እያንዳንዱንም ሰው በየሥራው ላይ ይደልድሉት፤ ምን መሸከም እንዳለበትም ያስታውቁት። 20ቀዓታውያን ግን ንዋየ ቅድሳቱን ለአንድ አፍታ እንኳ ለማየት አይግቡ፤ ቢገቡ ይሞታሉ።”

ጌድሶናውያን

21 እግዚአብሔር (ያህዌ) ሙሴን እንዲህ አለው፤ 22“ጌድሶናውያንንም በየቤተ ሰባቸውና በየጐሣቸው ቍጠራቸው፤ 23ከሠላሳ እስከ አምሳ ዓመት የሆናቸውን በመገናኛው ድንኳን ውስጥ ይሠሩ ዘንድ ለማገልገል የሚመጡትን ወንዶች ሁሉ ቍጠር።

24“የጌድሶናውያን የሥራና የሸክም አገልግሎታቸው ይህ ነው፤ 25እነርሱም የማደሪያውን መጋረጃዎች፣ የመገናኛውን ድንኳን፣ መደረቢያውንና በላዩ ላይ ያለውን የአቆስጣ ቍርበት፣ የመገናኛውን ድንኳን ደጃፍ መጋረጃዎች ይሸከሙ፤ 26እንዲሁም በማደሪያውና በመሠዊያው ዙሪያ ያሉትን የአደባባዩን መጋረጃዎች፣ የአደባባዩን ደጃፍ መጋረጃ፣ ገመዶችና ለዚሁ አገልግሎት የሚውሉትን ዕቃዎች ሁሉ ይሸከሙ፤ በዚህም ያገልግሉ። 27የጌድሶናውያን አገልግሎት ሁሉ፣ ሸክምም ሆነ ሌላ ሥራ አሮንና ልጆቹ በሚሰጡት አመራር መሠረት ይሆናል። የሚሸከሙትን ሁሉ በኀላፊነት ታስረክቧቸዋላችሁ። 28እንግዲህ የጌድሶናውያን ጐሣዎች በመገናኛው ድንኳን የሚኖራቸው አገልግሎት ይህ ነው፤ ተግባራቸውም በካህኑ በአሮን ልጅ በኢታምር አመራር ሥር ይሆናል።

ሜራሪያውያን

29“ሜራሪያውያንን በየጐሣቸውና በየቤተ ሰቦቻቸው ቍጠራቸው፤ 30እንዲሁም በመገናኛው ድንኳን ውስጥ ይሠሩ ዘንድ ለማገልገል የሚመጡትን ከሠላሳ እስከ አምሳ ዓመት የሆናቸውን ወንዶች ሁሉ ቍጠር። 31በመገናኛው ድንኳን ውስጥ አገልግሎቶቻቸውን በሚያከናውኑበት ጊዜ ተግባራቸው ይህ ነው፤ የማደሪያውን ሳንቃዎች፣ መወርወሪያዎች፣ ምሰሶዎችንና መቆሚያ እግሮቻቸውን፣ ይሸከማሉ፤ 32እንደዚሁም በአደባባዩ ዙሪያ ያሉትን ምሰሶዎች ከነመቆሚያ እግሮቻቸው፣ ካስማዎችን፣ ገመዶችን፣ ከእነዚሁ ጋር ያሉትን ዕቃዎች ሁሉና ማንኛውም ለአገልግሎቱ አስፈላጊ የሆኑትን ነገሮች ሁሉ ይሸከማሉ። እያንዳንዱ ሰው የሚሸከመውን ዕቃ ለይታችሁ በስሙ መድቡለት። 33እንግዲህ የሜራሪያውያን ጐሣዎች በካህኑ በአሮን ልጅ በኢታምር ሥር ሆነው በመገናኛው ድንኳን ሲሠሩ አገልግሎታቸው ይህ ነው።”

የሌዋውያን ጐሣዎች ቈጠራ

34ሙሴ፣ አሮንና የማኅበረ ሰቡ አለቆች ቀዓታውያንን በየጐሣቸውና በየቤተ ሰባቸው ቈጠሯቸው።
35ከሠላሳ እስከ አምሳ ዓመት ሆኗቸው በመገናኛው ድንኳን ውስጥ ለማገልገል የመጡት ወንዶች ሁሉ፣ 36በየጐሣቸው የተቈጠሩት ሁለት ሺሕ ሰባት መቶ አምሳ ነበሩ። 37ይህ ከቀዓት ጐሣዎች ሁሉ በመገናኛው ድንኳን ያገለገሉት ሰዎች ጠቅላላ ድምር ነው። ሙሴና አሮን፣ እግዚአብሔር (ያህዌ) በሙሴ አማካይነት በሰጠው ትእዛዝ መሠረት እነዚህን ቈጠሯቸው።

38ጌድሶናውያን በየጐሣቸውና በየቤተ ሰባቸው ተቈጥረው ነበር።
39በመገናኛው ድንኳን ውስጥ ይሠሩ ዘንድ ለማገልገል የሚመጡት ከሠላሳ እስከ ሃምሳ ዓመት የሆናቸው ወንዶች ሁሉ፣ 40በየጐሣቸውና በየቤተ ሰባቸው የተቈጠሩት ሁለት ሺሕ ስድስት መቶ ሠላሣ ነበሩ። 41ይህ ከጌድሶን ጐሣዎች በመገናኛው ድንኳን ያገለገሉት ሰዎች ጠቅላላ ድምር ነው፤ እግዚአብሔር (ያህዌ) በሰጠው ትእዛዝ መሠረት ሙሴና አሮን እነዚህን ቈጠሯቸው።

42ሜራሪያውያንም በየጐሣቸውና በየቤተ ሰባቸው ተቈጥረው ነበር።
43በመገናኛው ድንኳን ውስጥ ይሠሩ ዘንድ ለማገልገል የሚመጡት ከሠላሳ እስከ አምሳ ዓመት የሆናቸው ወንዶች ሁሉ፣ 44በየጐሣቸው የተቈጠሩት ሦስት ሺሕ ሁለት መቶ ነበሩ። 45ይህ የሜራሪ ጐሣዎች ጠቅላላ ድምር ነው፤ እግዚአብሔር (ያህዌ) በሙሴ አማካይነት በሰጠው ትእዛዝ መሠረት ሙሴና አሮን እነዚህን ቈጠሯቸው።

46ስለዚህ ሙሴ፣ አሮንና የእስራኤል አለቆች ሌዋውያኑን በየጐሣቸውና በየቤተ ሰባቸው ቈጠሯቸው፤ 47ከሠላሳ እስከ አምሳ ዓመት ሆኗቸው በመገናኛው ድንኳን ውስጥ አገልግሎት ለመስጠትና ለመሸከም የመጡት፣ 48ቍጥራቸው ስምንት ሺሕ አምስት መቶ ሰማንያ ነበሩ። 49እግዚአብሔር (ያህዌ) በሙሴ አማካይነት በሰጠው ትእዛዝ መሠረት እያንዳንዱ በየአገልግሎቱና በየሸክም ሥራው ተደለደለ፤ ስለዚህም እግዚአብሔር (ያህዌ) ሙሴን ባዘዘው መሠረት ቈጠራቸው።
Copyright information for AmhNASV